በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃውን የጠበቀ የታክሲና የብዙሃን ትራንስፖርት ተርሚናል ሊገነባ ነው፡፡

10 Jan 2019

በከተማዋ መገናኛ አካባቢ ደረጃውን የጠበቀ የታክሲና የብዙሃን ትራንስፖርት ተርሚናል ግንባታ ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡ የታክሲና የብዙሃን ትራስፖርት ተርሚናሉ ሲጠናቀቅም በሰዓት ከ25 ሺህ በላይ ህዝብ የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል፡፡ የተርሚናሉን ግንባታ በማስመልከት ከተገልጋዮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት በሞዛይክ ሆቴል በተካሄደው ውይይት እንደተገለጸው የተርሚናሉ መገንባት በርካታ የከተማዋን ህዝብ ተጠቃሚ በማድረግና ፣ የስራ እድል በመፍጠር ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ተመልክቷል፡፡ ተርሚናሉ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ርብርብ እንደሚያደርጉም ተገልጋዮችና ባለድርሻ አካላት አስታውቀዋል፡፡ የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሰመረ ጅላሉ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት የተርሚናሉ ግንባታ ለመጀመር የማቴሪያል ግዥ በጨረታ ሂደት ላይ እንደሆነ አመላክተው ጊዜያዊ የታክሲና የአውቶቡስ መጫኛና ማውረጃ ቦታ የማመቻቸት ስራም ተጠናቋል ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃቸውን የጠበቁ ተርሚናሎች እንደሌሏት አውስተው ሊገነባ የታሰበው ዘመናዊ ተርሚናል የከተማዋን ህብረተሰብ የትራንስፖርት ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡የግንባታ ስራው በሚቀጥሉት 3 ወራት ውስጥ እንደሚጀምርም ሃለፊው ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ለማስቻል የሚገነባው ዘመናዊ የታክሲና የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ተርሚናል በሰዓት በርካታ ህዝብ የትራንስፖርት ተጠቃሚ የሚያደርግ ከመሆኑም በተጨማሪ ተጠቃሚው ሁለንተናዊ አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ ከእንግልት የሚታደግ ነው፡፡ በውሰጡ የገበያ ማእከል፣ ካፌና መዝናኛ እንዲሁም ከተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮች ጋር ተሳስሮ የሚገነባ መሆኑ ተርሚናሉ ተመራጭ እንደሚያደርገው ኢንጂነር ሰመረ አስረድተዋል፡፡ አክለውም በከተማዋ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በታቀደው መሠረት አጠቃላይ የግንባታ ሁኔታውን በተመለከተ ከተገልጋዮች እና ከባለድርሻ አካላት ግብዓት ለመውሰድ የምክክር መድረክ ማዘጋጀት ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም በመድረኩ የተነሱ የተለያዩ ሃሳቦችና ጥያቄዎች በግብአትነት መወሰዴን ጠቁመው የተርሚናሉ ግንባታ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በሚወስደው የሁለት ዓመት ጊዚያት የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ በግንባታው ሂደት ለሚፈጠሩ ጊዜያዊ መጉላላቶች ህብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠባበቅ ዋና ስራ አስኪያጁ አስገንዝበዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው በሰጡት አሰተያየት በተለይ ከታክሲ ማህበራትና ከተራ አስከባሪዎች ዘንድ ይነሳ የነበረው ቅሬታ በፕሮጀክቱ ምላሽ ያገኙ ስለሆነ ለተርሚናሉ ግንባታ ስራ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ባለስልጣን የየካ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ደምሴ ታዬ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በሚገነባበት አከባቢ የሚኖሩና የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንደመሆናቸው ከህብረተሰቡ ጋር የመግባባቱን ስራ ቀድመው መጨረሳቸውንና ግንባታውን ለማስጀመርም የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም የተርሚናል ግንባታ ሲጀምር ጊዜያዊ አገልግሎት የሚሰጡ ቦታዎችን የማመቻቸት ስራም ከህብረተሰቡ ጋር በመግባባት እየተሰራ መሆኑን አቶ ደምሴ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ዘገባው፦ የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው 011557 32 66