ሚዛናዊ ስኮር ካርድን በአግባቡ በመጠቀም ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም ሰራተኛ በኃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀስ ይገባል ተባለ

10 Jan 2019

ተለይተው የወጡ ማነቆዎችን በለውጥ ሠራዊት ትግበራ ውስጥ በማካተት ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም ሰራተኛ በኃላፊነት መንፈስ እንዲንቀሳቀስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ጥሪ አቀረበ። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮና የትራንፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሰራተኞች በሚዛናዊ ስኮር ካርድ ምንነት፣ አዘገጃጀትና አተገባበር የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት አካሂደዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የክትትልና ድጋፍ ሲኒየር ኦፊሰር አቶ አብርሃም አድነው በውይይቱ ወቅት እንዳብራሩት ሚዛናዊ ስኮር ካርድን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ የተወጠኑ ዕቅዶችን ወደ ውጤት በመለወጥ የመፈጸም ብቃት ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡ ሚዛናዊ ስኮር ካርድን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ በስራ ላይ ሊከሰቱ ለሚችሉ ተግዳሮቶችን በመቀነስ ሁሉም ሰራተኛ ውጤታማ ስራ ማከናወን የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ውጤታማነትን ለማስመዝገብ ከዕቅድ ዝግጀት እስከ ትግበራና ምዘና ድረስ ያለውን ሂደት እያንዳንዱ ፈጻሚና አስፈጻሚ በሚገባ ጨብጦ ለመፈጸምና ለማስፈጸም መትጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ አያይዘውም ግቦችና የግብ ውጤቶች የተናበቡ አለመሆን፣ ዓመታዊ የግቦች ውጤትን ከአምስቱ ዓመት ዕቅድ አንጻር እየገመገሙ የተደረሰበትን ደረጃ አለማወቅ እና ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ ግብ ተኮር ተግባራትን በመለየት መርሀ-ግብር አለማዘጋጀት ተጠቃሽ ማነቆዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም የዕቅድ ዝግጅት ትግበራው፣ አፈጻጸሙና አመዛዘኑ በራሱ ከስትራቴጅክ ዕቅድ የሚመነጭ በመሆኑ፣ ዕለት በዕለት የሚሠሩ ተግባራት በዕውቀት ላይ በመመሥረት መከናወን ስለሚገባቸው በሚዛናዊ ስኮር ካርድ ላይ የጠራ ግንዛቤ መጨበጥ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሚዛናዊ ስኮር ካርድ ስራ ማሳለጫ ችግር ፈቺ እንዲሆን መሰረታዊ የስራ ሂደት የለውጥ ጥናት፣ የዜጎች ቻርተር እና ካይዘን የለውጥ መሳሪያዎች የማይተካ ሚና ያላቸው መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የስትራቴጂያዊ ሚዛናዊ ስኮር ካርድ ዕቅድ አዘገጃጀት ሂደት ላይ ወጥ የሆነ አረዳድ አለመኖር፣ የዕቅድ አዘገጃጀት ጥራት ያለው አለመሆን እና የግቦች፣ መለኪያዎችና ኢላማዎች አለመተሳሰር እንደተግዳሮት የሚያጋጥሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ሚዛናዊ ስኮር ካርድን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ የመፈጸም ብቃት ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ጠቁመው ተለይተው የወጡ ማነቆዎችን በለውጥ ሠራዊት ትግበራ ውስጥ በማካተት ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም ሰራተኛ በኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ዘገባው፦ በትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው ለበለጠ መረጃ፦ 011 557 32 66