የኢትዮጵያን አንድነት እና ሰላም ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት ተባለ

10 Jan 2019

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት በይበልጥ በማፋጠን የኢትዮጵያን አንድነት እና ሰላም ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለባት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት ቢሮና የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሰራተኞች አስታወቁ፡፡ ሠራተኞቹ 13ኛውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በፓናል ውይይት አክብረዋል። “ብዝሃነት፣ መቻቻልና እርቅ ለአገራዊ አንድነት ግንባታ” በሚል ርዕስ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል። ሰራተኞችም በፓናል ውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማስተሳሰር የህዝቦችን አንድነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ አክለውም በህዝቦች መካከል ያለውን መስተጋብር ይበልጥ ለማጠናከር የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ ለአንድ አገር ዕድገት ሰላም የማይተካ ሚና መኖሩን የገለጹት ሰራተኞች የአገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገትና ሰላም ለማስቀጠል ልዩነቶችን በማጥበብ ችግሮችን በእርቅ መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የቢሮ ኃላፊው ልዩ ረዳት አቶ ወርቁ ደስታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ በዘለቄታዊ መንገድ ለመመለስ በቅርቡ ባደረገው ጥልቅ ተሃድሶ ተከታታይ የሆነ ሥር ነቀል ፖለቲካዊ የማሻሻያ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ አቶ ወርቁ አያይዘውም በተወሰደው ስር ነቀል እርምጃ የፖለቲካ ድባቡን ከመቀየርም ባሻገር ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ ከፍ አድርጎታል ብለዋል፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ምህዳሩን የማጥበብ ሚና የተጫወቱ ሕጎችን የማሻሻል ሥራም መጀመሩ የተናገሩት አቶ ወርቁ የኢትዮጵያን አንድነት እና ሰላም ማጠናከር የሚያስችሉ የፍትህና የፀጥታ ተቋማትን ጨምሮ ሠፋ ያለ ተቋማዊ የመዋቅር ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የለውጥ ስራዎች ክትትል፣ ድጋፍና ምዘና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ተስፋየ አለባቸው በበኩላቸው በሀገራችን እየታየ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ በህብረተሰቡ መካከል ግጭት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት የፈጠሯቸው ግጭቶች በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ተስፋየ በማያያዝም አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችን በአባቶቻችን የቆየ ልማድና ባህል እንዲሁም እየተገነባ ባለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመፍታት አብሮነትንና አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡ በሀገራችን የሚቻቻልና የሚከባበር ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ የመገንባት ሥራን መንግሥት በዋናነት የመምራት ሃላፊነት ቢኖርበትም፣ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ሊሸከመው የሚገባ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ 13ኛው የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክብረ በዓል “በብዝኃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡ ዘገባው፦ በትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው ለበለጠ መረጃ፦ 011 557 32 66