Menu

  አማርኛ       English                

የሥራ አስኪያጁ መልዕክት

ዓለም በዉድድር ምህዋር ላይ እየተሸከረከረች ባለችበት በአሁኑ ሰዓት ሀገሮች በምጣኔ ሀብት (ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ንግድ፣ ወዘተ)፣ በጦር መሣሪያ፣ በቴክኖሎጂ፣ በዜጎች አኗኗር፣ እና በመሳሰሉት አንዱ ከሌለኛዉ ተሽሎ ለመገኘት የሚያደርጉትን እልህ አስጨራሽ ፉክክር እንታዘባለን፡፡

በዚህ ዉድድር ዉስጥ ሀገሮች በተለያዩ ዘርፎች ነጥረዉ የወጡበትና ለጊዜዉም ቢሆን አንጻራዊ የበላይነታቸዉን ያረጋገጡበት ሁኔታ መኖሩንም ማየት ይቻላል፡፡ ለአብነትም አሜሪካ በህዋ፣ በጦር መሣሪያ እና በኤኮኖሚ ያላትን አንጻራዊ የበላይነት እንዲሁም ሩሲያ፣ እስራኤልና አሜሪካ በደህንነት ዙሪያ ያላቸዉን ቀዳሚነት ማንሳት ይቻላል፤ ሌሎችም እንዲሁ፡፡

ከነዚህ የየዘርፉ ስኬቶች በስተጀርባም ጥናትና ምርምር የሚያካሄዱ፣ አቅጣጫዎችን የሚያሳዩ፣ የመፍትሄ አማራጮችን በሳይንሳዊ የመረጃ ትንተና የሚያቀርቡ፣ በአጠቃላይ ለየዘርፉ ስኬት ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ የምርምር ተቋማትን እናገኛለን፡፡ የአሜሪካዉ ናሳ (NASA) በተለያዩ ዘርፎች እንዲሁም የደቡብ ኮሪያዉ ኮቲ (KOTI) በትራንስፖርት ዘርፍ ያስመዘገቡትን ስኬት ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

 የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የትራንስፖርት ዘርፉን በከፍተኛ የቴክኒክ ብቃት በመምራትና በማስተባበር ብሎም የተለያዩ ፕሮግራሞችንና ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና በመተግበር የከተማዋን የትራንስፖርት ሥርዓት አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ወጪ ቆጣቢና አከባቢያዊ ተስማሚነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን ለማስቻል የተቋቋመ ተቋም ነዉ፡፡

የከተማዋን የትራንስፖርት ሥርዓት ጽኑ መሠረት ለመጣል በሚደረገዉ ጥረት ዉስጥ በጽቤቱ የተለያዩ ጥናቶች ይደረጋሉ፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ይቀመራሉ፣ የከተማዋ የረጅምና የአጭር ጊዜ ስትራቴጂዎችና እቅዶች ይነደፋሉ፣ ከተለያዩ ሀገራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ የዘርፉ ባለድርሻ አካለትና የምርምር ተቋማት ጋር ያለዉ የሥራ ግንኙነት ይዳብራል፣ ወዘተ፡፡

በዚህ ሂደት የሠራተኛዉ ክህሎት እየዳበረ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ እንደ ከተማዋ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም በተደራጀ መልኩ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ለዉጥ ማምጣት የሚችል ብቃት ያለዉ ተቋም ይፈጠራል ብለን እናምናለን፡፡ ይህ ተቋም በሀገርም ሆነ በአህጉር ደረጃ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ በሚያደርገዉ ጥናትና ምርምር ተጠቃሽና ተምሳሌት እንደሚሆንም እናምናለን፡፡ እንደዛሬዉ የደቡብ ኮሪያዉ KOTI ነገ ላይ ኢትዮጵያዊ ስመ-ጥር ተቋም እንዲኖረን እናልማለን፤ ለዚህም ተግተን እንሰራለን፡፡

አማርኛ