Menu

  አማርኛ       English                

የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

አካል:

በከተማዋ መገናኛ አካባቢ ደረጃውን የጠበቀ የታክሲና የብዙሃን ትራንስፖርት ተርሚናል ግንባታ ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡ የታክሲና የብዙሃን ትራስፖርት ተርሚናሉ ሲጠናቀቅም በሰዓት ከ25 ሺህ በላይ ህዝብ የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል፡፡ የተርሚናሉን ግንባታ በማስመልከት ከተገልጋዮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት በሞዛይክ ሆቴል በተካሄደው ውይይት እንደተገለጸው የተርሚናሉ መገንባት በርካታ የከተማዋን ህዝብ ተጠቃሚ በማድረግና ፣ የስራ እድል በመፍጠር ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ተመልክቷል፡፡ ተርሚናሉ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ርብርብ እንደሚያደርጉም ተገልጋዮችና ባለድርሻ አካላት አስታውቀዋል፡፡ የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሰመረ ጅላሉ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት የተርሚናሉ ግንባታ ለመጀመር የማቴሪያል ግዥ በጨረታ ሂደት ላይ እንደሆነ አመላክተው ጊዜያዊ የታክሲና የአውቶቡስ መጫኛና ማውረጃ ቦታ የማመቻቸት ስራም ተጠናቋል ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃቸውን የጠበቁ ተርሚናሎች እንደሌሏት አውስተው ሊገነባ የታሰበው ዘመናዊ ተርሚናል የከተማዋን ህብረተሰብ የትራንስፖርት ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡የግንባታ ስራው በሚቀጥሉት 3 ወራት ውስጥ እንደሚጀምርም ሃለፊው ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ለማስቻል የሚገነባው ዘመናዊ የታክሲና የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ተርሚናል በሰዓት በርካታ ህዝብ የትራንስፖርት ተጠቃሚ የሚያደርግ ከመሆኑም በተጨማሪ ተጠቃሚው ሁለንተናዊ አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ ከእንግልት የሚታደግ ነው፡፡ በውሰጡ የገበያ ማእከል፣ ካፌና መዝናኛ እንዲሁም ከተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮች ጋር ተሳስሮ የሚገነባ መሆኑ ተርሚናሉ ተመራጭ እንደሚያደርገው ኢንጂነር ሰመረ አስረድተዋል፡፡ አክለውም በከተማዋ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በታቀደው መሠረት አጠቃላይ የግንባታ ሁኔታውን በተመለከተ ከተገልጋዮች እና ከባለድርሻ አካላት ግብዓት ለመውሰድ የምክክር መድረክ ማዘጋጀት ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም በመድረኩ የተነሱ የተለያዩ ሃሳቦችና ጥያቄዎች በግብአትነት መወሰዴን ጠቁመው የተርሚናሉ ግንባታ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በሚወስደው የሁለት ዓመት ጊዚያት የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ በግንባታው ሂደት ለሚፈጠሩ ጊዜያዊ መጉላላቶች ህብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠባበቅ ዋና ስራ አስኪያጁ አስገንዝበዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው በሰጡት አሰተያየት በተለይ ከታክሲ ማህበራትና ከተራ አስከባሪዎች ዘንድ ይነሳ የነበረው ቅሬታ በፕሮጀክቱ ምላሽ ያገኙ ስለሆነ ለተርሚናሉ ግንባታ ስራ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ባለስልጣን የየካ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ደምሴ ታዬ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በሚገነባበት አከባቢ የሚኖሩና የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንደመሆናቸው ከህብረተሰቡ ጋር የመግባባቱን ስራ ቀድመው መጨረሳቸውንና ግንባታውን ለማስጀመርም የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም የተርሚናል ግንባታ ሲጀምር ጊዜያዊ አገልግሎት የሚሰጡ ቦታዎችን የማመቻቸት ስራም ከህብረተሰቡ ጋር በመግባባት እየተሰራ መሆኑን አቶ ደምሴ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ዘገባው፦ የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው 011557 32 66

አካል:

ኢ/ር ታከለ ኡማ "የተደራጀ እና የተቀናጀ አመራር ለውጡን በብቃት ለመምራት!" በሚል መርህ ቃል በተዘጋጀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች የግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ ተገኝተዋል፡፡ ከንቲባ ታከለ ኡማ ለአመራሮቹ ባደረጉት ንግግር ላይ "የበቃ እና ህዝብን የወገነ አመራር ለውጡን የማስቀጠል አቅም ይኖረዋል ብለዋል፡፡" በተጨማሪም አመራሩ ለውጡን በመቀበሉ ረገድ በግምባር ቀደም መቆም እንዳለበት፣ ለወጣቶች እና ሴቶች የስራ እድል በሚፈጠርበት ሁኔታ እና በአገልግሎት አሰጣጥ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራርያ የሰጡ ሲሆን ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው አመራሩ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡ ሶስተኛ ቀኑን በያዘው በዚሁ መድረክ ላይ ከ1500 የሚሆኑ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን በሁሉም ሴክተሮች የታዩ ደካማ አተገባበሮችን በመቅረፍ ህብረተሰብ ተኮር የሆኑ ተግባራት ላይ አተኩሮ መስራት እንዳለበት ተጠቅሷል፡፡

አካል:

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት በይበልጥ በማፋጠን የኢትዮጵያን አንድነት እና ሰላም ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለባት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት ቢሮና የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሰራተኞች አስታወቁ፡፡ ሠራተኞቹ 13ኛውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በፓናል ውይይት አክብረዋል። “ብዝሃነት፣ መቻቻልና እርቅ ለአገራዊ አንድነት ግንባታ” በሚል ርዕስ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል። ሰራተኞችም በፓናል ውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማስተሳሰር የህዝቦችን አንድነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ አክለውም በህዝቦች መካከል ያለውን መስተጋብር ይበልጥ ለማጠናከር የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ ለአንድ አገር ዕድገት ሰላም የማይተካ ሚና መኖሩን የገለጹት ሰራተኞች የአገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገትና ሰላም ለማስቀጠል ልዩነቶችን በማጥበብ ችግሮችን በእርቅ መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የቢሮ ኃላፊው ልዩ ረዳት አቶ ወርቁ ደስታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ በዘለቄታዊ መንገድ ለመመለስ በቅርቡ ባደረገው ጥልቅ ተሃድሶ ተከታታይ የሆነ ሥር ነቀል ፖለቲካዊ የማሻሻያ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ አቶ ወርቁ አያይዘውም በተወሰደው ስር ነቀል እርምጃ የፖለቲካ ድባቡን ከመቀየርም ባሻገር ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ ከፍ አድርጎታል ብለዋል፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ምህዳሩን የማጥበብ ሚና የተጫወቱ ሕጎችን የማሻሻል ሥራም መጀመሩ የተናገሩት አቶ ወርቁ የኢትዮጵያን አንድነት እና ሰላም ማጠናከር የሚያስችሉ የፍትህና የፀጥታ ተቋማትን ጨምሮ ሠፋ ያለ ተቋማዊ የመዋቅር ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የለውጥ ስራዎች ክትትል፣ ድጋፍና ምዘና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ተስፋየ አለባቸው በበኩላቸው በሀገራችን እየታየ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ በህብረተሰቡ መካከል ግጭት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት የፈጠሯቸው ግጭቶች በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ተስፋየ በማያያዝም አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችን በአባቶቻችን የቆየ ልማድና ባህል እንዲሁም እየተገነባ ባለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመፍታት አብሮነትንና አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡ በሀገራችን የሚቻቻልና የሚከባበር ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ የመገንባት ሥራን መንግሥት በዋናነት የመምራት ሃላፊነት ቢኖርበትም፣ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ሊሸከመው የሚገባ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ 13ኛው የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክብረ በዓል “በብዝኃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡ ዘገባው፦ በትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው ለበለጠ መረጃ፦ 011 557 32 66